ቀጥታ፡

በክልሉ በመኸር አዝመራ ከለማው ሰብል ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት ይሰበሰባል

ጋምቤላ፤ ሕዳር 15/2018(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል በመኸር አዝመራ ከለማው ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደሚሰበሰብ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የምርት ብክነትን ለማስቀረት በባለሙያ የታገዘ ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ቢሮው ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አንዲሪው ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት ፤ በምግብ ራስን ለመቻልና ከተረጂነት ለመላቀቅ እንደ ሀገር ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።


 

የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ግብ ለማሳካትም በክልሉ ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ በ2017/18 የመኸር እርሻ ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱንና ከዚህም ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ በተደረገው የምርት ግምገማ ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

የዘንደሮው የመኸር እርሻ ከቀዳሚው ዓመት ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት በመልማቱና ሰብሉም በጥሩ ቁመና ላይ በመሆኑ ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማሰማራት የደረሰ ሰብል የምርት ብክነት በማያስከትል መልኩ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በተለይም አርሶ አደሮችን በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሃብቶችና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በማስተሳሰር በመፈልፈያ ማሽኖች ምርታቸውን ጊዜ በሚቆጥቡና ብክነት በሚያስቀር መልኩ እንዲሰበስቡ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የእርሻ ዘርፍና የሰብል ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወለጋ ኡሎክ በበኩላቸው፤ በክልሉ በመኸር አዝመራ 172 ሺህ 239 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 184 ሺህ ሄክታር መልማቱን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅትም በቆሎን ጨምሮ ቀድመው የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ እንደሚገኙ ጠቁመው በእስካሁኑ ሂደት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።

ከመንግስት ስራቸው ጎን ለጎን በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ኡቦንግ ኡንግሊ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለቤተሰብ የምግብ ፍጆታ የሚሆን ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ገልጸዋል።


 

የምግብ ዋስትና በቤተሰብና በአካባቢ ደረጃ እንዲረጋገጥ መንግስት ለያዘው ግብ መሳካት ሁላችንም መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም