ማንችስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን ጋር ይጫወታል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ 19 ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ጎሎችን አስተናግዷል።
ዩናይትድ በ18 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኤቨርተን በበኩሉ ከ11 ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 12 ግቦችን በጨዋታዎቹ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
የመርሲሳይዱ ክለብ በ15 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሩበን አሞሪም የሚመራው ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ መልካም የሚባል ጅማሮ አድርጓል። ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። ይህም በአሞሪም ስር ሲሳካ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ተጋጣሚው ኤቨርተን አምና ካሳለፈው ጥሩ ያልሆነ የውድድር ዓመት በኋላ ዘንድሮ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
ዴቪድ ሞይስ በድጋሚ ወደ ቡድኑ ከመለሰ በኋላ መሻሻል አሳይቷል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለ61ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 60 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 37 ጊዜ ሲያሸንፍ ኤቨርተን 10 ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 13 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ በጨዋታዎቹ 111 ግቦችን ሲያስቆጥር ኤቨርተን 56 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የዛሬው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቶኒ ሃሪንግተን ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።