በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል ቶተንሃም ሆትስፐርስን በማሸነፍ የሊጉ መሪነት አጠናከረ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል ቶተንሃም ሆትስፐርስን በማሸነፍ የሊጉ መሪነት አጠናከረ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 14/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር አርሰናል ቶተንሃም ሆትስፐርስን 4 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኤቤሬቺ ኤዜ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
ሊያንድሮ ትሮሳርድ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ሪቻርልሰን ለቶተንሃም ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።
በጨዋታው አርሰናል በተጋጣሚው ላይ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።
ሀትሪክ የሰራው ኤቤሬቺ ኤዜ የጨዋታ ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል ነጥቡን ወደ 29 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል።
አርሰናል የነጥብ ልዩነቱን ከተከታዩ ቼልሲ በስድስት፣ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንችስተር ሲቲ በሰባት አስፍቷል።
በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ18 ነጥብ ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ዝቅ ብሏል።
ዛሬ በተደረገው ሌላኛው መርሃ ግብር አስቶንቪላ ከሜዳው ውጪ ሊድስ ዩናይትድን 2 ለ 1 አሸንፏል።
የፕሪሚየር ሊጉ የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገ ማንችስተር ዩናይትድ እና ኤቨርተን በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ