ቀጥታ፡

ታዳሽ ኃይል መጠቀም የሚያስችል የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሥርዓት በመዘርጋት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል መጠቀም የሚያስችል የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሥርዓት በመዘርጋት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስቴሩ ከፓወር አፍሪካ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ሁለተኛው ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2025 ኤግዚቢሽንና ባዛር ከታኅሣሥ 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ያካሂዳል፡፡


 

ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ሁለተኛውን ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2025 ኤግዚቢሽንና ባዛር ለማካሄድ በተደረጉ ዝግጅቶችና በሚጠበቁ ውጤቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት መተግበር የጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መደላድል እየፈጠረ ነው።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ኢትዮጵያ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(COP32) እንድታስተናግድ እንድትመረጥ አድርጓታል ሲሉም ገልጸዋል።

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ታዳሽ ኃይልም ሆነ ዝቅተኛ በካይ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከታኅሣሥ 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ ኤግዚብሽንና ባዛር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

በኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ላይ ኤሌክትሪክን ጨምሮ የተለያዩ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪ አምራቾች፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የጥናትና ምርምር ተቋማት እንደሚሳተፉ አብራርተዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ በጋራ ውይይት የሚደረግበት መርሐ ግብር መሰናዳቱንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም