ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ የወጣቶች፣ የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኮሚሽኑ

ሰመራ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የወጣቶች፣ የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ በሰመራ ከተማ "የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉደተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የስልጠና መድረክ ተጠናቋል።


 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በወቅቱ እንደተናገሩት ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ሚና የጎላ በመሆኑ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የሀገራዊ ምክክሩን ዓላማ ለማስረዳት መድረኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

የሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉደተኞች አደረጃጀትን በመጠቀም የምክክሩን ዓላማ የተመለከቱ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለአደረጃጀቶች የተሰናዳው ስልጠናም ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ያላቸውን የጎላ ሚና  ለማሳካት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰላም እጦት ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው ችግሮችን በምክክር ለመፍታትና ሰላምን ለማጠናከረ በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑንም ኮሚሽነሯ አንስተዋል።

የማያግባቡ ሀሳቦችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የተጀመረው ጉዞ እንዲሳካ የማህበረሰብ ክፍሎቹ የላቀ  ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ከዱብቲ ወረዳ የመጡት አቶ ተስፋዬ አዳነ በቀጣይ በሚካሄድ የምክክር መድረክ ተሳትፏቸውን በማጠናከር ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ ሀሳቦችን በማቅረብ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።


 

ከአርጎባ ልዩ ወረዳ የመጣው ወጣት የሱፍ መሐመድ በበኩሉ መድረኩ በታሪክ አጋጣሚ የተገኘና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መሰረት የሚጥል ነው ብሏል።

ወጣቶች ነገ የሚረከቧትን ሀገር ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት መሰል የውይይት መድረኮች በመሳተፍ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው ገልጿል።

በመድረኩ በንቃት በመሳተፍ ለምክክሩ ስኬታማነት ሀሳብ ከማዋጣት ባለፈ ታች ድረስ ወርዶ ወጣቶችን በማስተማር ኀላፊነቱን እንደሚወጣም ተናግሯል።


 

በተለያዩ አደረጃጀቶች አማካኝነት ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲጠናከሩና አካታች ሀሳቦች እንዲፈልቁ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ከሲቪክ ማህበር የመጡት ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ ናቸው።

ሴቶችን የተመለከቱ ሀሳቦች መፍትሄ እንዲያገኙ በመድረኩ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በተጨማሪ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚዲያ ተቋማት ተወካዮችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም