በሁምቦ ወረዳ ጠበላ ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የወተት ምርታማነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሁምቦ ወረዳ ጠበላ ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የወተት ምርታማነትን አሳድጓል
ጠበላ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ በሁምቦ ወረዳ ጠበላ ከተማ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የወተት ምርታማነትን ማሳደጉን በከተማው በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሦስት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭ ከተማ ያበሰሩት የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ይገኛል።
መርሀ ግብሩ ደካማ የአምራችነት ታሪክን በመቀየር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ አድገትን የማፋጠን ግብ አለው።
በዋናነት በወተት፣ በሥጋ፣ በእንቁላል፣ በማር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የቤት ውስጥ ፍጆታን ለማሟላትና እንደሀገርም በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው።
መርሀ ግብሩ በወላይታ ዞን በከተማና በወረዳ ጭምር ተግባራዊ ሆኖ በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የርሆቦት ቁጥር ሁለት ማህበር ሰብሳቢ ስንታሁ ጽጌ እንደገለጹት ለአምስት ሆነው በመደራጀት ከመንግስት በወሰዱት ብድር የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች እርባታ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በቀን እስከ 60 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ማድረሳቸውን ጠቁመዋል።
በዚሁ ሥራ ላይ የተሰማሩት ጋኔቦ ጎዳና በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የወተት ልማት ሥራቸውን በባህላዊ መንገድ ያከናውኑ እንደነበር አስታውሰው፣ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር መጀመሩን ተከትሎ ስራቸውን በተሻሻሉ የላም ዝርያዎች እያከናወኑና የተሻለ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ለሥራቸው ውጤታማነት በመንግስት በኩል ሙያዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸው፣ ከወተትና የወተት ተዋጽኦ ሽያጭ 3 ሚሊዮን ብር ሀብት ማፍራታቸውን ጠቁመዋል።
የጠበላ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ብሩክ ዮሴፍ በበኩላቸው ከሌማት ትሩፋት መርሃግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የወተት፣ የሥጋ፣ የማር፣ የዓሣ እንዲሁም የዶሮና እንቁላል መንደር መመስረቱን ጠቁመዋል።
በከተማው ከተመሰረቱ 50 የወተት መንደሮች መካከል 20ዎቹ ወደ ሥራ መግባታቸው ተናግረዋል።
ይህም በከተማው የእንስሳት ተዋፅኦን ምርታማነት በማሳደግ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ለከተማው ነዋሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ አስችሏል ብለዋል።
በዘርፉ የተሰማሩትን ማህበራት ውጤታማ ለማድረግ የገበያ ትስስር በመፍጠርና የገንዘብ ብድር በማመቻቸት ድጋፍ መደረጉም ጠቁመዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዞኑ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን እያገዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሙሉጌታ ኩታፎ ናቸው።
በዞኑ መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት ከ2015 ዓ.ም ወዲህ በርካታ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ውጤትም እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዞን በተቋቋሙ የወተት መንደሮች 55ሺህ 660 ዜጎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።