በክልሉ የደረሰ ሰብልን በዘመናዊ ማሽኖች ታግዞ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የደረሰ ሰብልን በዘመናዊ ማሽኖች ታግዞ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል
ወላይታ ሶዶ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደረሱ ሰብሎችን በዘመናዊ ማሽኖች ታግዞ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ከመከላከል ባለፈ የምርት መጠንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት እስከ 70 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በወላይታ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የመኸር ሰብል ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
ኃላፊው በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በመኸር ወቅት ለምተው ቀድመው የደረሱ ሰብሎች ምርት መሰብሰብ ተጀምሯል፡፡
የምርት አሰባሰብ ሂደቱን በዘመናዊ ማሽኖች በማገዝ ብክነትን ከመከላከል ባለፈ የምርት መጠኑንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በክልሉ በመኸር እርሻ ከለማው ከ840ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ እስከ 70 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ከ232ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በክላስተር የለማ ሲሆን፣ አርሶ አደሮችም የደረሱ ሰብሎችን በጋራ እንዲሰበስቡ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የምርት ብክነትን በመከላከል ምርታማነትን ያሳድጋል።
ውጤታማ የሰብል ስብሰባ ሥራ ለማከናወን አርሶ አደሩንና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የድጋፍ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና አሰራርን በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትን ለማደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የደረሰ የመኸር ሰብልን ከብክነት በጸዳ መልኩ በኮምባይነር ታግዞ ለመሰባሰብ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በመኸር የለማው ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ቀድሞ የደረሰውን ከብክነት በጸዳ መልኩ የመሰባሰብ ሥራ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ(ዶ/ር) ናቸው፡፡