ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው - ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር

ጅማ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ከፍተኛ መሆኑ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ገለጹ።

ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ሚና እና አስተዋጽኦ በተመለከተ በጅማ ከተማ የውይይት መድረክ አካሄዷል።

በመድረኩ ከአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ ከኢሉአባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ጅማ ዞኖችን ጨምሮ ከጅማ ከተማ የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ ውይይት በተለያዩ አካባቢዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸውን አጀንዳዎችና ጥያቄዎች በማካተት ለሀገራዊ ምክክሩ ግብአት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።

በሀገራችን ሰላም ለማስፈንና የተሻለ መረጋጋት ለመፍጠር ሁሉን አሳታፊ የምክክር መድረክ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለምክክሩ ስኬታማነት የሴቶች የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የካተተ የውይይት መርሃ ግብር  ማዘጋጀቱ ያልተነሱ ሀሳቦችን ለማንሳት አግዞናል ብለዋል።


 

ከተሳታፊዎቹ መካከል ዋቅጋሪ ሶሮማ ከነቀምቴ ከተማ የአካል ጉዳተኞችን ወክለው ለውይይቱ መሳተፋቸውን ገልጸው በዚህ መድረክ የምፈልገውን ሀሳብ የመጠየቅ እድል አግኝቻለው ሲሉ ተናግረዋል


 

ከጅማ ዞን የተወከሉት ወይዘሮ ጀሚላ ጣሃ በበኩላቸው በአካታች ውይይትና በምክክር የትኛውም ችግር ይፈታል የሚል እምነት ስላላቸው አጀንዳ በማስያዝ በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ሴቶችና ወጣቶች በርካታ ጥናቄዎች ያላቸው መሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ ተገቢነት እንዳለውም ተናግረዋል።

ወጣቱንና አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ ውይይት መደረጉ ያልተነሱ ጉዳዮችን ለማንሳት እድል የሚሰጥ ስለሆነ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተናል ብለዋል።

ትናንት የተጀመረውና ኮሚሽነሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም