የባህልና ኪነጥበብ ቡድኑ ጉዞ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የባህልና ኪነጥበብ ቡድኑ ጉዞ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል የባህልና ኪነጥበብ ቡድን ወደ ህንድ የሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ።
የአማራ ክልል የባህል እና ኪነጥበብ ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል በህንድ ሀገር በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የባህል እና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ ይሳተፋል።
ለቡድኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬና የዘርፉ አመራሮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሽኝት ተደርጎለታል።
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በዚሁ ወቅት፤ የባህልና ኪነጥበብ ቡድኑ የሀገሪቱን ባህላዊ ሀብቶች የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን በህንድ ሀገር ያቀርባል ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን መልካም ገጽታ ከመገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ቡድኑ የሚያቀርባቸው ሙዚቃዊ ቴአትሮችና የጥበብ ክዋኔዎች የኢትዮጵያን ብዝኃነትና የባህል እሴቶች የሚያንጸባርቁ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
ይህም የሀገርን ገጽታ በመገንባት ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና የሀገሪቱን እውነተኛ ገጽታ በአካል እንዲመለከቱ ያስችላል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ የአፍሪካዊነትና የኢትዮጵያዊነትን አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድጋል ነው ያሉት።
የባህልና ኪነጥበብ ቡድኑ አባላት ከጥበብ ትርኢት ባሻገር በመድረኩ ኢትዮጵያን በመወክል የአምባሳደርነት ሚና እንደሚጫወቱም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ባህል ኪነጥበባትና ዝክረ ታሪክ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ገብረማርያም ይርጋ በበኩላቸው፥ የባህል ቡድኑ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ሀገራት የኪነጥበብ ስራዎች ማቅረቡን አስታውሰዋል።
በህንድ ሀገር በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የባህል እና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ ቡድኑ የኢትዮጵያን ባህል፣ እሴትና አብሮነት የሚያሳዩ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ከባህል እና ኪነጥበብ ቡድኑ አባላት መካከል ወልደአረጋይ ዳዴ እና ሐመልማል ተክሉ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች የባህል አልባሳትና ዕደ-ጥበብ፣ ባህላዊ ውዝዋዜና ሙዚቃን ለማቅረብ ሰፊ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ የባህልና ኪነጥበብ ሥራዎችን እንደሚያቀርቡም ጠቁመዋል።