የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን አብሮነትና በጋራ የመልማት ፍላጎትን እያጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን አብሮነትና በጋራ የመልማት ፍላጎትን እያጠናከረ ነው
ጋምቤላ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን አብሮነትና በጋራ የመልማት ፍላጎት እያጠናከረ መሆኑን የጋምቤላ፣ ኦሮሚያና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተጎራባች አካባቢ ነዋሪዎችና አመራሮች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ 20ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በጋምቤላ ከተማ ባከበሩበት ወቅት እንዳሉት ቀኑ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ለጋራ ልማትና እድገት መነሳሳትን የፈጠረ ነው።
ከታዳሚዎቹ መካካል ከቄለም ወለጋ ዞን የመጡት ሃደ ሲንቄ አስቴር ሩፌ በሰጡት አስተያየት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የእርስ በርስ ግንኙነታችንና አብሮነታችንን እንድጠናክር እያዳረገ ነው ብለዋል።
የጋምቤላና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ህዝቦች ለዘመናት የቆየ የህዝብ ለህዝብና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁምው፤ ቀኑን በጋራ ማክበራቸው አብሮነታቸውንና ህብረታቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናከር ገልጸዋል።
ቀኑን ከኦሮሚያና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ተጎራባች አካባቢዎች በጋራ ማክበራቸው ትብብራቸውና አንድነታቸውን ይበልጥ ያጠናክራል ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪው ቄስ ማቲዎስ ዶሌክ ናቸው።
የአዋሳኝ አካባቢ ህዝቦች ህብረትና ትብብር መጠናከር ለአካባቢያቸው ዘላቂ ልማትና እድገት የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
በዓሉን ለመታደም የኢሉ አባቦራ ዞንን በመወከል የተገኙት ሰለሞን በቀለ እንዳሉት የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን የእርስ በርስ ግንኙነትና አብሮ የመልማት ፍላጎት እያጠናከረ ነው ብለዋል።
በዓሉን የተጎራባች ክልሎች ተዋሳኝ አካባቢዎች በጋራ ማክበራቸው አንድነታቸውና አብሮነታቸውን በማጠናከር የልማት ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
በመድረኩ የታደሙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ጌታቸው ኬኒ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህዝቦችን ይበልጥ በማቀራረብ ለጋራ ልማት እንዲተጉ እያደረገ ነው ብለዋል።
የጋምቤላ፣ የኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተጎራባች አካባቢዎች ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ የታደሉ አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በጋራ ማክበራቸው የልማት ትብብራቸውን ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።