ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉዳያችንን በአጭር ግዜ መጨረስ አስችሎናል - ተገልጋዮች

ሀዋሳ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ መጨረስ እንዳስቻላቸው በሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች ገለጹ።

በሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የ12 ተቋማት 38 አገልግሎቶች እየተሰጠ መሆኑን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ከጀመረበት መስከረም አጋማሽ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለ1ሺህ 300 ሰዎች አገልግሎት መስጠቱ ተገልጿል።

በማዕከሉ የሲዳማ ክልል ንግድ ቢሮ፣ ገቢዎች ባለስልጣን፣ ጤና ቢሮ እና የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ የ12 ተቋማት አገልግሎቶች በማዕከሉ ይሰጣሉ።

እነዚህ ተቋማት በአንድ ማዕከል ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠታቸው እንግልት፣ አላስፈላጊ ወጪና ጊዜ በመቆጠብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም ተገልጋዮች ገልጸዋል።

ኢዜአ በማዕከሉ ጉዳያቸውን ሲያስፈጽሙ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንደገለጹት ቀደም ሲል በተበታተነ ስፍራ ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ውስጥ ማግኘታቸው ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ መጨረስ አስችሏቸዋል።


 

በማዕከሉ አገልግሎት ለማግኘት የመጡት ወይዘሮ የሺመቤት ተረፈ እንዳሉት ቀደም ሲል በተለያዩ ቦታዎች ሲሰጡ የነበሩ የመንግስት አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የማዕከሉ አገልግሎት ረጅም ውረፋ ከማስቀረት ባለፈ የተገልጋይን እንግልትና የሚባክን ጊዜ ማስቀረቱን ገልጸዋል።


 

ውክልና ለመስጠት ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ እንደመጡ የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጪ ሄኖክ አደራ በበኩላቸው በማዕከሉ ፈጣን አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከበር ጀምሮ ጥሩ መስተንግዶ ማግኘታቸውን ጠቁመው፣ ማዕከሉ ከቀበሌ ጀምሮ ወደ ተለያዩ ተቋማት ሲመላለሱ ሲገጥማቸው የነበረን እንግልት የበዛበት አሰራርን ማስቀረቱንና ባገኙት አገልግሎት መደሰታቸውን ገልጸዋል።


 

በማዕከሉ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ተቋማት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ባለሙያ እንዳሻው ኤራንጎ ቀደም ሲል ደንበኞች ቲን ቁጥር ለማግኘት ወደ ባለስልጣኑ ሲመጡ አሻራ ሰጥተው የፋይዳ መታወቂያ እንዲያወጡ ኢትዮ ቴሌኮም እንልካቸው ነበር ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚሰጡ ተገልጋዩ ሁሉንም አገልግሎቶች  በማዕከሉ እያገኘ በመሆኑ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እንግዳየሁ ዘውዴ እንዳሉት በማዕከሉ 12 የፌዴራል፣ የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ተቋማት 38 አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።

ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ እስካሁን ድረስ ለ1ሺህ 300 ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰው፣ ተገልጋዩ ባገኘው አገልግሎት ላይ በሰጠው አስተያየትና እርካታ እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም