ባለስልጣኑ ዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት ተገልጋዩ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ ዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት ተገልጋዩ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል
ድሬዳዋ፣ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ የትራስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ እየተጋ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን ገለፀ።
በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና የመድን ፈንድ ዳይሬክተር ኢንጂነር ሁሴን ጀማል ለኢዜአ እንደገለፁት፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቶችን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው።
በተለይም አዲሱ የድሬዳዋ መናኸሪያ ተርሚናል በዘመናዊ መንገድ መገንባቱና ዲጂታል አገልግሎቶች ተደራሽ መደረጋቸው ቀደም ሲል የነበሩ ትርምሶችና መጨናነቆችን አስቀርቷል ብለዋል።
የጉዞ ትኬት በኢ-ቲኬቲንግ አሰራር መቀየሩ፣የትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ ቅጣታቸውን በቴሌብር እንዲከፍሉ መደረጉ ከዚህ በፊት ይባክን የነበረን የስራ ጊዜና ጉልበት ማስቀረት አስችሏል ብለዋል።
በተለይም ተጓዦች በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያቀርቡ ለነበሩት የተጋነነ የትራንስፖርት ክፍያን በመከላከል ፍትሃዊ እና ተደራሽ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።
እንደ ኢንጂነር ሁሴን ገለፃ፥ ባለስልጣኑ የጀመራቸውን የዲጂታል አገልግሎቶች በማሳደግ ስማርት ድሬዳዋን የሚመጥን አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል።
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ዘውገ አውላቸው በበኩላቸው፥ የዲጂታል አገልግሎቶቹ ከድሬዳዋ ወደ ተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በሚወጡና በሚገቡ የህዝብ ትራንስፖርቶች እና በከተማዋ ታክሲዎች ላይ ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።
አሽከርካሪዎች ጉዳያቸውን ካሉበት ስፍራ ሆነው በዲጂታል አገልግሎቱ እየተጠቀሙ ይገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጥን በዲጂታል ካሜራ በመከታተል ብቃትና ስነምግባር የተላበሱ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከድሬዳዋ-ሐረር ህዝብ የሚያመላልሰው የሚኒባስ አሽከርካሪ አቶ ሰይፈዲን አልይ እና የታክሲ አሽከርካሪው አቶ ጋሻው ሀብታሙ እንዳሉት፥ ባለስልጣኑ የጀመራቸውን የዲጂታል አገልግሎቶች ጊዜንና ጉልበትን ለስራ በማዋል ውጤታማ ስራ ለመስራት አስችሏቸዋል።
አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ከግማሽ ቀን በላይ ማባከን ቀርቷል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ይኸም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባ ብለዋል።