መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሚያዚያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሁሉም አካባቢ እንደሚስፋፋ ገልጸው ነበር።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር)፥ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ልዩ ልዩ የመንግስት አገልግሎቶችን ዘመኑን በዋጀና በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ የሚሰጥበትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታትን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
በመንግስት ተቋማት በሚሰጡ አገልግሎቶች የሚነሱ ቅሬታዎችን በጥራትና በፍጥነት ለመመለስ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህም እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 75 የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ ብቁ የሰው ኃይል የማዘጋጀት፣ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ማዕከላት በቴክኖሎጂና በመሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች የሚበረታቱ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽኑም ለስራው ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በዚህ ዓመት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን 100 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸው ይታወቃል።