በምስራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ22ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ22ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል
ደብረ ማርቆስ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ ባለፉት አራት ወራት ከ22ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ ስራና ስልጠና መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ተወካይ ሃላፊ ሙሉሰው አወቀ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የአካባቢውን ጸጋ በጥናት በመለየት ወጣቶችን በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱም ከ131ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን በተደረገ ጥረት ለ22ሺህ 267 ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
የስራ እድሉን መፍጠር የተቻለውም በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በንግድ፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ በምግብና ምግብ ነክ እንዲሁም ሌሎች የስራ ዘርፎች መሆኑን ተናግረዋል።
ከተፈጠረው የስራ እድል ውስጥም ከ12ሺህ በላይ የሚሆኑት በቋሚ ቀሪዎቹ በጊዜያዊነት ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልከቷል።
በኢንተርፕራይዞች የስራ እድል ለተፈጠረላቸ ወጣቶችም ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ከ140 በላይ ሼዶችና ኮንቲነሮች እንዲሁም 17 ሄክታር መሬት ለመስሪያና መሸጫ ማተላለፉንም አስገንዝበዋል።
የስራ እድሉ ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል የአዋበል ወረዳ የሉማሜ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኤርሚያስ መሰንበት እንዳለው ከአራት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በዶሮ እርባታ የስራ ዘርፍ ተሰማርተዋል።
ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ ከሶስት ሺህ በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማስገባት እያረቡ እንደሚገኙ ጠቁመው እንቁላል መጣል ሲጀምሩ ተጠቃሚነታቸው እንደሚያድግ ተናግሯል።
የዚሁ ወረዳ የሰንበት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ባየልኝ ያዜ በበኩሉ አምስት ጓደኛሞች ሆነው በመደራጀት ከግማሽ ሄክታር በላይ መሬት ወስደው የጓሮ አትክልት እያለሙ እንደሚገኙ ተናግሯል።
እያለሙት ያለው የጓሮ አትክልት ጎመን፣ ቲሚቲምና ቀይ ስር አሁን ላይ ለሽያጭ በመድረሱ እስከ 80 ሺህ ብር ገቢ እንደሚጠብቁም ተናግሯል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ115 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።