ቀጥታ፡

አስተዳደሩ ውድድሩ እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ይበልጥ ተጠቃሽና ተተኪዎች የሚፈሩበት እንዲሆን አበክሮ ይሠራል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ አስተዳደሩ በቀጣይም ይህ ውድድር እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ይበልጥ ተጠቃሽና ተተኪዎች የሚፈሩበት እንዲሆን ይበልጡኑ አበክሮ ይሠራል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት ተወዳጁን፣ ተናፋቂውንና ባለፉት 25 ዓመታት የከተማችን አንዱ ድምቀት እና አለም አቀፍ መገለጫ የሆነውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በልዩ ድምቀት አስጀምረናል ብለዋል።


 

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም ኮከብ አትሌቶች መለማመጃ፣ መኖሪያ በሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ፣ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከፕሮፌሽናል አትሌት እስከ ጤና ቡድኖች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እየተሳተፈበት፣ እየተዝናናበት፣ ጤናውን እየጠበቀበት፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትንና አብሮነትን እያጠናከረበት 25 የድምቀት ዓመታትን አሳልፏል ነው ያሉት።


 

የዚህ ታላቅ ውድድር መስራች የሆነውን ጀግናው አትሌታችንን ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴን፣ እንዲሁም አጠቃላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አመራሮችን ባለሙያዎችንና አስተባባሪዎችን ለዘመን ተሻጋሪ ሥራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

አስተዳደራችን በቀጣይም ይህ ውድድር እንደ ሌሎችም ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ይበልጥ ተጠቃሽና ተተኪዎችን ጭምር የምናፈራበት እንዲሆን ይበልጡኑ አበክሮ ይሠራል ሲሉም ገልጸዋል።


 

ተሳታፊዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለውድድሩ ስኬት ለነበራችሁ በጎ አስተዋፅኦ ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም