ቀጥታ፡

245ኛው የኢንተር እና የኤሲ ሚላን የደርቢ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 14/2018 (ኢዜአ) ፦ በጣልያን ሴሪአ የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ጨዋታው በሳንሲሮ ስታዲየም ምሽት 4 ሰዓት ከ45 ላይ ይከናወናል።

ኢንተርሚላን በሊጉ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ 26 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ24 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የከተማ ተቀናቃኙ ኤሲ ሚላን በውድድር ዓመቱ 11 ጨዋታቸውን አድርጎ በስድስቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።

17 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረውበታል። ሚላን በ22 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ245ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 244 ጨዋታዎች ኢንተር ሚላን 91 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኤሲ ሚላን 82 ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪዎቹ 71 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በሴሪአው 182 ጊዜ ተገናኝተው ኢንተር ሚላን 70፣ ኤሲ ሚላን 55 ጊዜ አሸንፈዋል። 57 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ባለፉት 10 የሴሪአ ግንኙነታቸው ኢንተር ሚላን ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ኤሲ ሚላን ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በሁለቱ ጨዋታዎች አቻ ወጥተዋል።

ክለቦቹ ለ116 ዓመታት የዘለቀ ተቀናቃኝነት አላቸው። ኢንተር ሚላን 20 እና ኤሲ ሚላን 19 ጊዜ የሴሪአ ዋንጫን አንስተዋል።

በአህጉራዊ መድረክም ኤሲ ሚላን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ሰባት ጊዜ በማንሳት ስኬታማው ክለብ ነው። ኢንተር ሚላን ሶስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።

ኢንተር ሚላን ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ከናፖሊ ይረከባል። በአንጻሩ ኤሲ ሚላን ድል ከቀናው ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደርጋል።

የ38 ዓመቱ ሲሞኒ ሶዛ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም