ቀጥታ፡

የአርሰናል እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ የሰሜን ለንደን ደርቢ ፍልሚያ 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የሊጉ መሪ አርሰናል ከተቀናቃኙ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ስታዲየም የሚያደርጉት ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የቡድኖቹ ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ 60 ሺህ 704 ተመልካች በሚያስተናግደው ኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

አርሰናል በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።

በጨዋታዎቹ 20 ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ግቦችን አስተናግዶ በ26 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከ11 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፎ በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹም 19 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎች ተቆጥረውበት በ18 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የሰሜን ለንደኖቹ አርሰናል እና ቶተንሃም ሆትፐርስ 129 ዓመታትን ያስቆጠረ የተቀናቃኝነት ታሪክ አላቸው።

ቡድኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙነት እ.አ.አ በ1896 ሲሆን በወቅቱ ዩናይትድ ሊግ በሚባለው የውድድር ፎርማት ላይ ተጫውተው አርሰናል (በወቅቱ አጠራሩ ዎልዊች አርሰናል) ቶተንሃም ሆትስፐርስን 2 ለ 1 አሸንፏል።

እ.አ.አ በ1897 በዩናይትድ ሊግ ተገናኝተው ቶተንሃም ሆትስፐርስ 3 ለ 2 በማሸነፍ በአርሰናል ላይ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

ቡድኖቹ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረው ተቀናቃኝነታቸው እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 211 ጊዜ ተገናኝተዋል።

በዚህም አርሰናል 89 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ቶተንሃም ሆትስፐርስ 67 ጊዜ አሸንፎ 55 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ 66 ጊዜ ባደረጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አርሰናል 27 ጊዜ ሲያሸንፍ ቶተንሃም ሆትስፐርስ 15 ጊዜ ድል ቀንቶት 24 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው አርሰናል አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

ጠንካራ የመከላከል አቅም፣ ሚዛኑን የጠበቀ ተጭኖ የመጫወት ስልት እና የታክቲክ ብስለት የአርሰናል የዘንድሮ የጥንካሬ መገለጫዎች ናቸው።

ቡድኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለፈጣን መልሶ ማጥቃት ተጋላጭ የሆነባቸውን ሁኔታዎች ዘንድሮ ለመመልከት ተችሏል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በፈጣን የክንፍ የመስመር ተጫዋቹ የሚያደርገው ጠንካራ እና ፍሰት ያለው የማጥቃት እንቅስቃሴ ለተጋጣሚዎች አስፈሪ ነው።

በአንጻሩ ወጥነት የጎደለው የተከላካይ መስመሩ ተጋላጭነት እንደ ድክመት የሚነሳ ነው።

ብራዚላዊው ወሳኝ የአርሰናል ተጫዋች ጋብርኤል ማጋሌስ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ መራቁ ለመድፈኞቹ ጥሩ ዜና አይደለም።

ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎም ይጠበቃል።

የ40 ዓመቱ ማይክል ኦሊቨር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በሌላኛው የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሊድስ ዩናይትድ ከአስቶንቪላ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም