ህብረተሰቡን በተሻለ ብቃት፣ ታማኝነትና ቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅተናል - የፖሊስ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡን በተሻለ ብቃት፣ ታማኝነትና ቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅተናል - የፖሊስ መኮንኖች
ቦንጋ ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፦ህብረተሰቡን በተሻለ ብቃት፣ በታማኝነትና ቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመረቁ የፖሊስ መኮንኖች ገለጹ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሞድዮ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም የመካከለኛና ከፍተኛ አመራር መኮንኖች የምረቃ መርሃ-ግብር ዛሬ ተከናውኗል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖሊስ መኮንኖች እንደገለፁት በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ህብረተሰቡን በተሻለ ብቃት፣ ታማኝነትና ቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅተዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ረዳት ኢንስፔክተር መላኩ ማለቶ እና ረዳት ኢንስፔክተር ጌታቸው ገብሬ፣ በስልጠና ቆይታቸው ወቅቱን የሚመጥን እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በፖሊስነት ሙያ ከአስር ዓመት በላይ ማገልገላቸውን የገለፁት ረዳት ኢንስፔክተር ባንቻየሁ ተስፋዬ በበኩላቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ይህን እድል አመቻችቶ ስልጠና እንድናገኝ ማድረጉ የተሰጠንን ኃላፊነት በላቀ ብቃት እንድንወጣ ተጨማሪ አቅምን ይፈጥርልናል ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሳ፤ የፖሊስ አመራሮችና አባላትን የሚዲያና ቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ ለህብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ኃይልና ጠንካራ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በመሆኑም ፖሊስ ራሱን ከቴክኖሎጂ ጋር እያላመደና እያዋሀደ ወቅቱ የሚጠይቀውን እውቀት መታጠቅና ሌሎችንም ማስታጠቅ ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል።
ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖቹ ለፍትህ መስፈን በመትጋት ማኅበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ህገ-መንግስታዊ ሀላፊነታቸውን በላቀ ብቃት እንዲወጡም አሳስበዋል።