ቀጥታ፡

የባቡር አካዳሚው የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ጉልህ ድርሻ ያበረክታል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-የባቡር አካዳሚው መገንባት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት የትርንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

የትርንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሕሊና በላቸው በዛሬው እለት በቢሾፍቱ ከተማ ኪሎሌ ወረዳ የባቡር አካዳሚ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡


 

አካዳሚው የሚገነባው በቢሾፍቱ ከተማ ኪሎሌ ወረዳ ሲሆን፤ ግንባታው በ62 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ዘመናዊ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ ግብዓት ነው ብለዋል፡፡

ዘርፉን ቀልጣፋ እና ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሰላሳ ዓመታት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ፍኖተ ካርታ እና የአስር ዓመታት መሪ የልማት እቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሰፊ የመንገድ እና የባቡር መሰረተ ልማቶችን በመስራት ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የላቀ ሚና ስታበረክት መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

ዘመናዊ መንገዶችንና የባቡር መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት ጎን ለጎን ኢንዱስትሪውን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ የባቡር አካዳሚ ማቋቋም ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አካዳሚው ለኢንዱስትሪው የሰለጠነና የበቃ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡


 

አካዳሚው ስልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ባቡር የሚገጣጠምበት፣ ጥገና የሚደረግበትና ባቡር እስከማምረት የሚደርስ ርዕይ እንዳለው ጠቁመዋል።

ለአጎራባች ሀገራት ባለሙያዎች ስልጠናዎችን በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል እና ለስራ እድል ፈጠራ ሁነኛ አማራጭ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የባቡር አካዳሚው መገንባት የኢትዮጵያነ የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት  ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሕሊና በላቸው በበኩላቸው፤ የባቡር ትራንስፖርት የወጪ እና ገቢ ምርቶችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳልጥ ተናግረዋል።


 

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ እንደገለጹት፤ አካዳሚው ለከተማዋ በረከትና ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ያገለግላል።

በመሆኑም አካዳሚው በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም