ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የሰብል አሰባሰብ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የሰብል አሰባሰብ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ገንዳውኃ፣ ሕዳር13/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በምግብ ራስን የመቻል ፕሮግራም በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ሰብል የማሰባሰብ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ ዘላለም አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግስት የችግር ጊዜ እርዳታን በራስ አቅም በመሸፈን ተረጅነትን ዜሮ ለማድረግ ርብርብ እያደረገ ነው።
ይህም በምግብ ራስን የመቻል ፕሮግራም በዞኑ ስር ከሚገኙ ወረዳዎች በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ 110 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የምግብ እህል ለመሰብሰብ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፤ በተጨማሪም በክረምቱ ለዚሁ ዓላማ በተለያየ የሰብል ዘር ከተሸፈነው 300 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ከሰባት ሺህ 800 ኩንታል በላይ የማሽላ ምርት የሚጠበቅ መሆኑንም አመልክተዋል።
የምግብ እህል ክምችቱ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
የምግብ ሉዓዊነትን በማረጋገጥ ተረጅነትን ዜሮ ለማድረግ በመንግስት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ዞኑ የድርሻውን ለመወጣት ርብርብ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
በመተማ ወረዳ ድጋፍ ከሚሹ ወገኖች መካከል አቶ ማለደ ቢምረው በሰጡት አስተያየት፤ በሕብረተሰቡ እና በመንግሥት ድጋፍ ላለፉት አራት ዓመታት ችግር ሳይገጥማቸው ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
አሁን በመተማ ወረዳ ኩመር አፍጥጥ ቀበሌ የለማው ማሽላ ለወደፊት ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጓል ብለዋል።
በመተማ ወረዳ ኮኪት ቀበሌ አርሶአደር ደጀን አስማማው በበኩላቸው ፤ ለመጠባበቂያ ክምችት የሚጠበቅባቸውን ለማዋጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።