ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ሸገር ከተማ ድል ሲቀናው ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይተዋል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሸገር ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል። 

አምበሉ ሄኖክ አዱኛ በ97ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። 

በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ሸገር ከተማ በስምንት ነጥብ ደረጃውን ከ17ኛ ወደ 14ኛ ከፍ አድርጓል።


 

በአንጻሩ በሊጉ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በሶስት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ አላሸነፈም።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። 

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ12 ነጥብ አራተኛ፣ ድሬዳዋ ከተማ በ10 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል።


 

ፋሲል ከነማ የሊጉ መሪ የመሆን እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በአሁኑ ሰዓት ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም