ሰላምን በዘላቂነት የማፅናት ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በዘላቂነት የማፅናት ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
ደሴ/ ወልዲያ/ ደብረ ብርሃን፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት እያከናወኑት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
"ዘካሪና መካሪ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላምና ለልማት" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጁ የምክክር መድረኮች ዛሬ በደሴ፣ ወልዲያና ደብረ ብርሃን ከተሞች ተካሂዷል።
የመድረኮቹ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፤ በክልሉ ሰላምን አበክረው በመስበክ በዘላቂነት የማፅናት ተግባርን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
በደሴ ከተማ በተካሄደው ምክክር ተሳታፊ ቄስ መላኩ አየለና ሼህ ይማም አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ከሁሉም በፊት ሰላምን ማፅናት ያስፈልጋል ብለዋል።
አብሮነታቸውን በማጎልበተ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የከተማቸውን ሰላምና ልማት አጠናክረው ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም አስታውቀዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የከተማውን ሰላም በማፅናት ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለዚህም የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመው፤ ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በአካባቢያችን የተገኘውን ሰላም ለማፅናት እያደረግን የምንገኘውን ጥረት ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ በወልድያ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አባ አያሌው ሲሳይ እና አቶ አለሙ የሱፍ ናቸው።
የወልዲያ ከተማ ከንቲባ የአቅም ግንባታ አማካሪ ወይዘሮ አስናቀች ኃይሌ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም መፅናት እገዛቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው መድረክም መላከ ሰላም ምስራቅ ሲሳይ እና አቶ አህምየ መሐመድ፤ የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልና ልማትን ለማረጋገጥ ሕብረተሰቡን በማስተባበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከሕዝብ ጋር በተደጋጋሚ የተደረጉ ውይይቶች መልካም ውጤት ማስገኘታቸውን ተናግረዋል።
የከተማዋን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በከተሞቹ በተካሄዱ የውይይት መድረኮች የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የከተሞቹ አመራሮች ተሳትፈዋል።