በእንስሳት ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በእንስሳት ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዳማ ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- በእንስሳት ሀብት ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ101ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ8ኛ ጊዜ የተከበረውን የእንስሳት ቀን በማስመልከት በአዳማ ከተማ ዛሬ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ፤ የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመን የተለያዩ ኢንሼቲቮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተለይ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ፣ በመኖ ልማት፣ በእንስሳት ጤናና ደህንነት ላይ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።
የእንስሳት ቀኑን ከማሰብ ባለፈ የእንስሳት ሀብቱ ላይ በተለይ ወተትና የወተት ተዋፅኦ እንዲሁም የስጋ ምርት ውጤታማነት ላይ ውይይት በማካሄድ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል ።
ሚኒስቴሩ በእንስሳት ሀብት ውጤታማነት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ለዚህም የእንስሳት ጤና ስትራቴጂና የማስፈፀሚያ ስልቶች በመቅረፅ በተለይ የእንስሳት ሀብቱን በዘመናዊ መንገድ ለማልማት የሚያግዙ ስራዎችን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ እንስሳት ሀኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ቦጂያ ሂንደቡ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የእንስሳት ጤናና ደህንነት አዋጅ መውጣቱን ጠቅሰው፤ ይህም የእንስሳት ጤና ሙያተኞች በዕውቀታቸው ዘርፉን እንዲደግፉ እድል የሰጠ ነው ብለዋል።
በተለይ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ላይ የተሻለ ሙያዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የሀብቱን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ባለድርሻ አካላት በእንስሳት ጤና አጠባበቅና ሀብትን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀረፁ ስትራቴጂዎች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎች ውጤታማ እንዲሆኑ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።