ደም እና የዓይን ብሌንን መለገስ የሁሉም ዜጋ ማህበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ደም እና የዓይን ብሌንን መለገስ የሁሉም ዜጋ ማህበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል
አዳማ ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- ደምና የዓይን ብሌንን መለገስ የሁሉም ዜጋ ማህበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ የደምና የዓይን ብሌን ልገሳን ለማሳደግ ያለመ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
በወቅቱም የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ አገልግሎቱ የደም እና የዓይን ብሌን ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ለዚህም ደምና የዓይን ብሌንን መለገስ የሁሉም ዜጋ ማህበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው፤ የአገልግሎቱን ተግባር ተረድተው ምላሽ የሚሰጡ ዜጎችን ቁጥር ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት የዓይን ብርሀናቸውን የማጣት አደጋ ላጋጠማቸው ዜጎች እይታን ለመመለስ እና ተስፋ ለመሆን አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
የዘንድሮውን የዓለም አቀፍ የዓይን ብሌን ቀንን በማስመልከት በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በዚህ ወር የዓይን ብሌን ልገሳ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።
ለዚህም ከሕልፈተ ሕይወት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የሚገቡ ሰዎች ቁጥርን ለማበራከት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክም አገልግሎቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት አንድ ሺህ 21 ሰዎች የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የአገልግሎቱ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።