ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለተኪ ምርት የተሰጠው ትኩረት የምርታማነት አቅምን እያሳደገ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ለተኪ ምርት የተሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅማቸውን እያሳደገ እንደሚገኝ አምራች ኢንዱስትሪዎች ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው ሀገር ሀቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማነቃቃት ምቹ መደላድል እየፈጠረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ታምርት ብሔራዊ ንቅናቄም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርት ጥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሻሻል ለሀገር ዕድገት ገንቢ ሚና እንዲወጣ እያደረገ ነው።


 

በአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ኢትዮጵያ የሚጠይቃትን የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት በርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው አድርጓል። 

ከኢዜአ ቆይታ ያደረጉ በምግብና መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችም፤ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅምን በማሳደግ ምቹ ዕድሎችን ፈጥሯል ብለዋል።

በአዳማ ከተማ የሚገኘው የቱብራዘርስ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አዩብ አረቦ፤ ለተኪ ምርት የተሰጠው ትኩረት የምርታማነት አቅማቸውን በማሳደግ ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪ የፈጠረው ምቹ መደላድልም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል። 

የቱብራዘርስ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የፈጠረው የምርታማነት አቅም ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በአዳማ ከተማ የአህዋን የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሰው ሃይል ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተርና የፋብሪካው የቦርድ አማካሪ ጅብሪል አሰፋ፤ ፋብሪካው ከ500 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። 


 

በመንግስት ፖሊሲ መነሻነት በተኪ ምርት የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ጥራታቸውን የጠበቁ የፓስታና መኮሮኒ ምርቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሸገር ከተማ አስተዳደር የፕሮማክሲዶር ኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አማረ አበራ፤ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሳደግ የማበረታቻ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።


 

በዚህም የምርታማነት አቅማቸውን በማሳደግ ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ዕድል እንደፈጠሩ ገልጸዋል።

በቱብራዘርስ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ዳዊት መኮንን፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ገልጿል።


 

በፋብሪካው የተፈጠረልኝ የሥራ ዕድል እራሴንና ቤተሰቤን የማስተዳድርበት ዕድል ተፈጥሮልኛል ያለችው ደግሞ የፕሮማክሲዶር ኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሠራተኛ ትብለጥ ከበደ ናት።


 

በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ደበበ ወርቁ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማበረታታት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

የአምራች ኢንዱስትሪ ድጋፍና ክትትልም ዘርፉ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት መፍትሔ በመስጠት የሀገር ውስጥ ተኪ ምርት አቅምን ማጎልበት እያስቻለ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም