ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በጥራትና በፍጥነት አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለህብረተሰቡ በጥራትና በፍጥነት አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻላቸው የሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ከበደ ሻሜቦ ገለጹ።

በሀገር  ደረጃ ከተነደፉ የተቋማት ማሻሻያ ፕሮግራም ውስጥ አንዱ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው።

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ጋዜጠኞች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ተገንብቶ ስራ የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።


 

የሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ሻሜቦ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በቅርቡ ስራ የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ አሰራርን መሰረት ያደረገ ነው ። 

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎቱ  60 አገልግሎቶችን መስጠት እንዲችል ሆኖ መገንባቱን ገልጸው፤ አሁን ላይ  በሰባት ተቋማት 20 አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ የተገልጋዩን መረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን አስችሏል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ይህም የመረጃ ደህንነትንና ተጠያቂነትን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የማህበረሰቡን የአገልግሎት ጥያቄ በመመለስ  የጥራት፣ የቅልጥፍና፣ የብልሹ አሰራር ችግሮችን በማስቀረት የአገልግሎት እርካታን ማሳደግ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

ህብረተሰቡ አገልግሎቶችን በፍጥነት እንዲያገኝ በማድረግ ጊዜንና ገንዘብን በመቆጠብ ረገድ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች እንደሚቋቋሙ ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም