ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ለዓለም የጋራ ውጥኖች መሳካት በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ለዓለም የጋራ ውጥኖች መሳካት በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ለዓለም የጋራ ውጥኖች እና ራዕዮች መሳካት በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የወቅቱ የቡድን 20 አባል ሀገራት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ እና የአባል ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የቡድን 20 ጉባኤ በአፍሪካ መደረጉ ታሪካዊ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው በመደመር እሳቤ ሁሉን አቀፍ ልማት እና እድገት ለማምጣት እየሰራች ነው ብለዋል።
የመደመር እሳቤ ትብብር፣ አካታችነት እና አቃፊነትን መሰረት ያደረገና ብዝሃ የሆኑ ምልከታዎችን የያዘ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድም ከተሞች የኢኖቬሽን ማዕከላት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኢኮኖሚ እድገት አቅም እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ የዲጂታል ዘርፍን የአካታችነት መሳሪያ አድርጋ እየተጠቀመች መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸው እና ገቢያቸው እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተሻግራ ህልሞቿን ማሳካት እንደምትችል በተግባር እያሳየች መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የማይበገር አቅም እየገነባች እንደሆነ ተናግረዋል።
ከችግር ይልቅ የመለወጥ ተስፋ ላይ በማተኮር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እያመጡ እንደሚገኙም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስት ጉዳዮች ትኩረት እንደሚያሻቸው አጽንኦት አንስተዋል።
በዚሁ መሰረት ዓለም አቀፍ የእዳ አስተዳደር ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፤ አበዳሪዎች በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የእዳ እፎይታ በመስጠት እና ተበዳሪ ሀገራት ብድርን ለልማት እና እድገት ስራቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በተጨማሪም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ኢኒሼቲቮችን ለሚተገብሩ ሀገራት እዳቸው በአካባቢ ስራቸው እንዲካካስ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል።
ዲጂታል ትራስፎርሜሽን፣ መሰረተ ልማት እና ኢኖቬሽን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሱ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካን በታዳሽ ኃይል የመልማት ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቡድን 20 አይበገሬነትን የእድገት መለኪያ አድርጎ እንዲቆጥረው የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጫናዎችን መቋቋም ራሱን የቻለ እድገት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም የጋራ ውጥኖች እና ራዕዮች መሳካት በመደመር እሳቤ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።