ቀጥታ፡

የምስራቅ ዕዝ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እየተወጣ በልማትም ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው

ሐረር፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፡- የምስራቅ ዕዝ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ከመወጣት በተጓዳኝ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።

በሐረር ከተማ የሚገኘውና እድሳት የተደረገለት የዕዙ ታሪካዊ የሐረር መኮንኖች ክበብ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ባደረጉት ንግግር፤ ዕዙ ሀገራዊ ተልዕኮውንና ግዳጁን በላቀ ብቃት አኩሪ  ገድል እያስመዘገበ የሚገኝ የሀገር አለኝታ ነው ብለዋል።

ዕዙ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና በልማቱ ስራ በመሳተፍ የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር ማሳየቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ለዚህም ሰራዊቱ የተገነባበት እሴቶችና የማይነጥፍ የሕዝብ ድጋፍ አስተዋፅኦ የጎላ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን ዕዙ በግብርና ስራዎች ላይ በመሰማራት በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተካሄደ ባለው ስራም ተጨባጭ ውጤት በማስገኘት እያገዘ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም በኮሪደር ልማት ስራውም በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ያሉት የዕዙ ዋና አዛዥ፤ ታሪካዊ ስፍራዎችንና ቅርሶችን የመንከባከብ ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

የእድሳት ስራውን በማጠናቀቅ በዛሬው እለት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የሐረር መኮንኖች ክበብ አንዱ ቅርስ መሆኑን  ጠቁመው፤ ዕዙ የሚያከናውነው የልማት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የምስራቅ ዕዝ የሰራዊት ስነ ልቦና ግንባታ ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ማርዬ ምትኩ በበኩላቸው፤  ከለውጡ ማግስት ጀምሮ  ትኩረት ተነፍገውና ተረስተው የነበሩ ታሪካዊ ስፍራዎችንና ወታደራዊ ቅርሶችን የመንከባከብ ስራዎች በትኩረት ተከናውነዋል ብለዋል።

በዚህም  ወደ ቀደመ ክብራቸው መመለስ መቻሉን  አክለዋል።


 

በ1937 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለት የሐረር መኮንኖች ክበብ ለመዝናኛነት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ስለ ሀገርና ሕዝብ ምክክር የሚደረግበት ስፍራ ሆኖ የቆየ ሲሆን ፤  በተደረገለት ሙሉ እድሳትና ጥገና ለሕዝብ  አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴራል፣የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ፣የዕዙ ከፍተኛ መኮንኖች፣ባለሃብቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም