በፎረሙ ለከተሞች እድገት እና ብልጽግና መሰረት የሚሆኑ ተሞክሮዎችን ቀስመናል-ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በፎረሙ ለከተሞች እድገት እና ብልጽግና መሰረት የሚሆኑ ተሞክሮዎችን ቀስመናል-ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ለከተሞች እድገት እና ብልጽግና መሰረት የሚሆኑ ተሞክሮዎች መቅሰማቸውን በ10ኛው የከተሞች ፎረም የተሳተፉ አካላት ገለጹ።
10ኛው የከተሞች ፎረም በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ መካሄዱ የሚታወቅ ሲሆን ከፎረሙ ጎን ለጎን በተካሄደው ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች ተሞክሯቸውን ለአቻ ከተሞች አጋርተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፎረሙ ታዳሚዎች በፎረሙ ለከተሞች እድገት እና ብልጽግና መሰረት የሚሆኑ ተሞክሮዎችን መቅሰማቸውን ገልጸዋል።
በሸገር ከተማ አስተዳደር የከተሜነት እና የከተሞች ትስስር ዳይሬክተር በዛ ቱሉ፤ የሸገር ከተማ በፈጣን የእድገት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው ነዋሪዎችን በማስተባበር ውጤታማ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሸገር ከተማ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታውቀው ፎረሙ በተለይም በአረንጓዴ ልማት ልምድ የተገኘበት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በዲጂታል አሰራር እና ቤቶች ልማት ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸው በቀጣይ ተሞክሮዎቹን በመቀመር ስራ ላይ እንደሚያውሏቸው አረጋግጠዋል።
የደሴ ልዑካን ቡድን ምክትል ሰብሳቢ ዳዊት በዛብህ በበኩላቸው፤ በደሴ ከተማ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማዋ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣አረንጓዴ ልማት እና የማረፊያ ሼዶችን ያካተተ የኮሪደር ልማት መከናወኑን ጠቅሰው የልማት ስራዎቹ የከተማዋን ገጽታ በጉልህ በመቀየር ለኑሮ ምቹ እያደረጓት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ፎረሙ በየከተሞች ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ለመቅሰም እንዳስቻላቸው ጠቁመው በተለይም በዲጂታል የመሬት አስተዳደር ምርጥ ተሞክሮ ማግኘታቸውን ነው ያስታወቁት።
ፎረሙ በከተሞች መካከል ውድድር እና ተነሳሽነት መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ልዑካን ቡድን አስተባባሪ ተረፈ ኡሜሳ ናቸው።
በሀዋሳ ከተማ ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ በተከናወኑ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከፍተኛ ስኬት መገኘቱን ጠቁመዋል።
የከተሞች ፎረም ከተሞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አስታውቀዋል።