ቀጥታ፡

የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች በመኸር ወቅት ያለሙትን  ሰብል ፈጥነው በመሰብሰብ ወደ መስኖ ልማት ገብተዋል

ወልዲያ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፡- በመኸር ወቅት አልምተው የደረሰውን ሰብላቸው ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመጠበቅ  ፈጥነው በመሰብሰብ ወደ መስኖ ልማት መግባታቸውን በሰሜን ወሎ ዞን  አርሶ አደሮች ተናገሩ።  

በሰሜን ወሎ ዞን በተያዘው  የበጋ ወቅት 14 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱን   የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል። 

አርሶ አደር ውበቱ አባተ በዘኑ የጉባላፍቶ ወረዳ ነዋሪ  ሲሆኑ፤ ባለፈው የመኸር ወቅት ያለሙትን የምግብ ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ከወዲሁ ለመከላከል ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበር ፈጥነው መሰብሰባቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ወደ መስኖ ልማት በመግባት ግማሽ ሄክታር የሚሆነውን መሬታቸውን በበጋ ስንዴ ዘር መሸፈናቸውን አስታውቀዋል።  

ልማቱን እያከናወኑ ያሉትን የምርት ግብዓቶችንና የግብርና ባለሙያዎች ምክር በመጠቀም መሆኑን አንስተው፤ በዘር ከሸፈኑት 16 ኩንታል የስንዴ ምርት  እንደሚጠብቁ  አስረድተዋል። 

አርሶ አደር ደሳለ ልሳነወርቅ በበኩላቸው የበጋ መስኖን በመጠቀም ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርትና ቲማቲም እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ይህም በመኸር ወቅት አልምተው የደረሰውን ሰብል ፈጥነው በመሰብሰብ እንደሆነ ተናግረዋል። 

የሽንኩርትና ቲማቲም ምርት ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን አርሶ አደሩ ጠቁመዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ወርቁ ደሳለ እንደገለጹት፤  በአካባቢው የበጋ መስኖ ልማት ላይ በማተኮር በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ ነው። 


 

እስካሁን 14 ሺህ 625 ሄክታር መሬት በማረስ 837 ሄክታር የሚሆነውን በስንዴ፣ ገብስ፣ ሽምብራና ሌሎች ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል። 

አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በሚካሄደው የመጀመሪያ ዙር   የበጋ መስኖ ልማት አንድ ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግም ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ወቅቱን ጠብቆ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በመኸሩ ወቅት ለምቶ የደረሰውን ሰብል  ፈጥኖ በማንሳት የመስኖ ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም