ዘመን ተሻጋሪ የሽምግልና እሴቶችን በመጠቀም ሰላምን ለማፅናት ሚናችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ዘመን ተሻጋሪ የሽምግልና እሴቶችን በመጠቀም ሰላምን ለማፅናት ሚናችንን እንወጣለን
ጎንደር፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ) ፡- በጎንደር ከተማ የሰፈነውን ሰላም ለማፅናት ዘመን ተሻጋሪ የሽምግልና እሴቶችን በመጠቀም ሚናቸውን እንደሚወጡ በከተማው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
"ዘካሪና መካሪ የሀገር ሽማግሌና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፤ የጎንደር ከተማ ሰላሟ ፀንቶ እንዲቀጥል ዘመን ተሻጋሪ የሽምግልና እሴቶችን በመጠቀም ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
አስተያየት ከሰጡት መካከል አቶ ሲሳይ ዘለቀ እንዳሉት፤ የዐጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና የጎንደርን ዳግም ትንሳኤ ያበሰረ ታላቅ ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡
የመነሳት የጉዞ ምዕራፍ ላይ የምትገኘውን የጎንደር ከተማ ያገኘችውን እድል ለማስቀጠል ዘመን ተሻጋሪ የሽምግልና እሴቶችን በመጠበቅ ሰላም እንዲፀና የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡
የከተማውን ሰላም በማፅናት የልማት ፕሮጀክቶችን የማስቀጠል ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ ቄስ ሞገስ ተስፋዬ ናቸው፡፡
የሃገር ሽማግሌ አቶ ተመስገን ደምሴ በበኩላቸው፤ የጎንደር ከተማን የቀደመ ስልጣኔ፣ ታሪኳና ክብሩዋን ዳግም ለመመለስ የተደረገው ጥረት ትልቅ ደስታን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የከተማው የኮሪደር ልማት፣ የመገጭ መስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ መንግስት ለከተማው እድገት መፋጠን የሰጠው ትኩረት ማሳያ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት፤ የከተማው ሕዝብ ሰላምና ልማት ወዳድነቱን በማሳየቱ የፌደራልና የክልሉ መንግስት ለከተማው ልማት መፋጠን ልዩ ድጋፍ እንዲያደርጉ አስችሏል።
የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገናን ጨምሮ በሁለት ምዕራፍ የተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ለከተማው ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶቹ ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥልና የተጀመሩ የልማት ስራዎችም እንዲጠናቀቁ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይም የከተማው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡