በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የፀረ- ፆታዊ ጥቃት ቀን (የነጭ ሪቫን ቀንን) አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ ኤርጎጌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ አሰራሮችን በመዘርጋት ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ዓለም አቀፍ የፀረ - ጾታዊ ጥቃት ቀን ዓላማ ህብረተሰቡን በማነቃነቅ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲወገድ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮ የፀረ - ጾታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ "ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከህዳር 15 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።
በመርሃ ግብሩ ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ዘዴዎች ግንዛቤ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት የሚያስችላቸው ስራ የሚሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ድጋፍ የሚሆን ሀብት የሚሰበሰብበት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም እውን ለማድረግ በፌዴራልና በክልሎች የተለያዩ ኮሚቴዎች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፉ የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን (የነጭ ሪቫን ቀን) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።