ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላምና ልማት በሚደረገው ጥረት ሚናችንን እናጠናክራለን - የሀገር ሽማግሌዎች

ባሕርዳር፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ለዘላቂ ሰላምና ልማት ቀጣይነት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚወጡ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

"ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌና የሀይማኖት አባቶች አባላት ለዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በባሕር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በዚሁ መድረክ ላይ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች፤ የሰላም ጉዳይ የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ በክልሉ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ቀጣይነት በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ጌትነት ተክለመስቀል፤ የሰላም ጉዳይ ሁላችንንም የሚመለከት የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ከሁሉም በላይ አብዝተን የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

በዚህም መሰረት ለከተማው ብሎም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት መሳካት ሚናቸውን አጠናክረን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ የሀገር ሽማግሌ አቶ ተስፋ አምባዬ፤ የከተማውና የአካባቢውን ሰላም ለማጠናከር የሁላችንም ሚና እና አስተዋጽኦ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

ሰላምን ማስጠበቅም ሆነ ልማትን ማፋጠን የሚቻለው የነቃ የሕዝብ ተሳትፎ ሲኖር ነው ያሉት የሀገር ሽማግሌው፤ ከግጭትንና ሁከትን በዘላቂነት ለመውጣት በጋራ መትጋት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፤ የከተማውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በተቀናጀ መልኩ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተው፤ የሕብረተሰቡ ትብብርና ተሳትፎም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

አሁን ላይ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጠው፤ ዘላቂ የማድረግ ስራ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በከተማዋ ሰላምን ከማፅናት በተጓዳኝ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶች፣ የአረንጓንዴ ልማት፣ የቱሪዝምና ሌሎችም የግንባታ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም