ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃል በገባው መሰረት የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀርመን አደባባይ ሳይት የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ግራር እና አየር ጤና ሳይቶች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መርቀዋል።
እነዚህም በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በፍጥነትና በጥራት በ24 ህንፃዎች የተገነቡትን 1 ሺህ 287 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች መሆናቸው ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በሰው ተኮር ስራዎች በርካታ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረጉን ገልጸው፤ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ በማድረግ ተመራጭ የመኖሪያ ስፍራ እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
የከተማዋን የመልማት ፍላጎት ለማርካት በርካታ ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የቤት አቅርቦት እና ፍላጎትን ለማጣጣም የሚያስችል የተለያዩ አማራጮች እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በግል አልሚዎች ፣በኪራይ፣ በማህበር፣ በግልና በመንግስት እና በሌሎች አማራጮች ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት እያደረግን ነው ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ከ380 ሺህ በላይ ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ከግል ባለሀብቶች ጋር የበለጠ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል።
በመፍጠር እና በመፍጠን የህዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆኑን ተናግረው፤ በዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ እና ሁሉንም መሰረት ልማት ያሟሉ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ፤ ዛሬ የተመረቁት ቤቶች ሁሉም መሰረት ልማቶች የተሟላላቸው እና ለመኖርያ ምቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ በጀርመን አደባባይ ሳይት 2 ቤዝመንት እና 15 ወለሎች ያሏቸው ህንጻዎች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።
የመናፈሻ፣ የአረንጓዴ ስፍራ፣ የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መሰረት ልማት መሟላታቸውንም ገልጸዋል።