የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
“አጋርነት፣ እኩልነት እና ዘላቂነት” ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ መሪ ሀሳብ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የወቅቱ የቡድን 20 አባል ሀገራት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ እና የአባል ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ይገኛል።
የዘንድሮው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ አካታች እና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
በጉባኤው የልማት ስራዎች ፋይናንስ፣ ዓለም አቀፍ የእዳ አስተዳደር እና ሁሉንም አባል ሀገራት እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ይካሄዳሉ።
መሪዎቹ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን፤ የንግድ ልውውጥን ማሳደግ እና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ትኩረት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ ፍትሃዊ የኢነርጂ ሽግግር በማረጋገጥ እና ጠንካራ ስርዓተ ምግብ በመገንባት ለጫናዎች የማይበገር ዓለምን የመገንባት ጉዳይም አጽንኦት ተሰጥቶታል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የዳታ አስተዳደር፣ ውድ ማዕድናት እና የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሌሎቹ የጉባኤው አጀንዳዎች ናቸው።
ቴክኖሎጂ እና ሀብቶች በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም ፍትሃዊ እና ዘላቂ ልማትን በተለይም በደቡብ የዓለም ንፍቀ-ክበብ እና በአፍሪካ ሀገራት ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይደረጋል።
የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ እስከ ነገ ይቆያል።