ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዳማ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፡- ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ።
በኦሮሚያ ክልል የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች አደረጃጀቶች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ባደረጉት ንግግር፤ በሀገራችን ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ኮሚሽኑ ዝግጅቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደትም ሴቶች ፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አንስተዋል።
የኮሚሽኑ ዓላማና ተግባር ላይ ዜጎች በቂና ግልጽ ግንዛቤ እንዲያገኙና ለምክክሩ ውጤታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከተቋማት፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከዲያስፖራውና ከሌሎችም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳ መሰብሰቡንም አንስተዋል።
የአዳማው መድረክም ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ምክክር በማከናወን ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን እየተደረገ ያለውን ተሳትፎ በማጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ መመቻቸቱን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው፤ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ምክክር ማስፈለጉን አንስተው፤ እስካሁን ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
መድረኩም ለቀጣዩ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የተሻላ ግንዛቤ ይዘው ተሳትፎዋቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሆነም አንስተዋል።