ቀጥታ፡

በምክክር ሂደቱ የሴቶች፣ ወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ ነው 

ጅማ፤ ህዳር 13/2018(ኢዜአ)፦ በምክክር ሂደቱ የሴቶች፣ ወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ሚና እና አስተዋጽኦ በተመለከተ በጅማ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ ከአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ ከኢሉአባቦራ፣ ከቡኖ በደሌ፣ ከደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞኖች፣ ከጅማ ከተማና ከዞኑ የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።


 

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ባለው የምክክር ሂደት የሴቶች፣ ወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተገቢው ሁኔታ እንዲሳተፋ እየተደረገ መሆኑን አንስተው የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር፤ የህብረተሰቡን አጀንዳዎች በመሰብሰብ ለዘላቂ መፍትሄ የምክክር ሂደት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት በተለይም የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በምክክሩ በማሳተፍ ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም እየሰራ መሆኑ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚም እድላቸውን በመጠቀም ለሀገራቸው ለመምከር ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከቡኖ በደሌ ዞን የተሳተፋት አቶ በዳሳ ሰዴታ፣ ከአጋሮ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ሩቂያ ከድር እና ከጅማ ከተማ አቶ ሰለሞን ይጥና፤ በምክክር መድረኩ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለጋራ ሀገራዊ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ኮሚሽነሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች የተሳተፉ ሲሆን ውይይቱ በነገው ዕለትም የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም