በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ኃይልና ጠንካራ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ኃይልና ጠንካራ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ቦንጋ፤ሕዳር 13/2018(ኢዜአ) ፦ በክልሉ በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ኃይልና ጠንካራ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ ማሠልጠኛ ተቋም የሁለተኛ ዙር የመካከለኛና ከፍተኛ ማዕረግ ሽግግር ሰልጣኞችን በዛሬው እለት አስመርቋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ፤በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የፖሊስ ኃይልና ጠንካራ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የፖሊስ ሙያ እራስን አሳልፎ በመስጠት ህዝብን ሌት ከቀን ማገልገልን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው ለዚህም በእውቀትና በቴክኖሎጂ የሚሰራ የሰው ሃይል ማፍራትን ይጠይቃል ብለዋል።
በዚህም መሰረት በዛሬው እለት በክልሉ ፖሊስ ማሰልጠኛ ስልጠና የተከታተሉ የሁለተኛ ዙር መካከለኛና ከፍተኛ ማዕረግ ሽግግር መደረጉ የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊስ መኮንኖቹም በስልጠና ቆይታቸው በቀሰሙት የላቀ እውቀትና ክህሎት ህዝብን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሳ፤ የፖሊስ አመራሮችና አባላትን ቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ ለህብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት ለምረቃ የበቁት የመካከለኛና ከፍተኛ ማዕረግተኞችም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አንስተው ወንጀልን በመከላከል ሰላምን በማስጠበቅ እንዲሁም ለልማት ስራዎች መሳካት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።