ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው 

ሠመራ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- ለሀገራዊ  ምክክሩ መሳካት የሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን ገለጸ። 

"የሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሃገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።  


 

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሸነር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የዳበሩ ሐሳቦችን በማቅረብ ሂደቱ እንዲሳካ ተሳትፎአቸው  ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። 

በሚፈጠሩ ችግሮች ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ተጎጂ እንደሚሆኑ አንስተው፤  ችግሮችና አለመግባባቶች በሰላም እልባት እንዲያገኙ ለማገዝ በምክክሩ ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በፌዴራልና ክልል ደረጃ የተካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራትን ወክለውና በራሳቸው ጉልህ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም አውስተዋል።

የሠመራው መድረክም ከዚህ በፊት ያልተሳተፉ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ግንዛቤ የሚያገኙበትና ምክረ ሐሳብ የሚሰጡበት መሆኑም ተመላክቷል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ከተለያዩ  ወረዳዎች የተውጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች እየተሳተፉ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም