ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ የባቡር አካዳሚ ልትገነባ ነው  

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ የባቡር አካዳሚ ልትገነባ ነው።

አካዳሚው የሚገነባው በቢሾፍቱ ከተማ ኪሎሌ ወረዳ ሲሆን፤ ግንባታው በ62 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሕሊና በላቸው፤ በቢሾፍቱ ከተማ ኪሎሌ ወረዳ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። 

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤  ከሁሉም አጎራባች ሀገሮች ጋር የሚያስተሳስሩ ዘመናዊ የባቡር መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት ጎን ለጎን ኢንዱስትሪውን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ለባቡር ኢንዱስትሪው የሰለጠነ የሰው ሃይል  በማፍራት ተተኪ ባለሙያዎችን የማሰልጠን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ የሚገነባው የባቡር አካዳሚ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኢንዱስትሪውን ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 

ለአጎራባች አገራት ባለሙያዎች ስልጠናዎችን በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሕሊና በላቸው በበኩላቸው፤ የባቡር ትራንስፖርት የወጪ እና ገቢ ምርቶችን እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳልጥ ተናግረዋል።

አካዳሚው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ቀጣናውን በትምህርት ዲፕሎማሲ እንደሚያስተሳስር ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ እንደገለጹት፤ አካዳሚው ለከተማዋ በረከትና ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ያገለግላል።

በመሆኑም አካዳሚው በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም