ቀጥታ፡

በክልሉ 68 ሺህ ዜጎችን የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

ባሕር ዳር ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፡-   በአማራ ክልል ባለፉት አራት ወራት  68 ሺህ  ዜጎችን የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።  

በርካታ ዜጎች  በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሄደው በመሥራት ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ለመደገፍ  መብቃታቸውም ተመልክቷል። 

ይህም  ከዚህ ቀደም በሕገ-ወጥ ደላሎች በመታለል  በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት በማስቀረት በኩል  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ተገልጿል።

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀምና በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በበጀት ዓመቱም ወጣቶች ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ በማድረግ ለአንድ መቶ ሺህ ዜጎች በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ተናግረዋል።

ዕቅዱን ለማሳካት በተደረገው ጥረትም ባለፉት አራት ወራት ብቻ ለ68 ሺህ ዜጎችን በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም ተግባር የተከናወነው ከሥራና  ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር  እንደሆነ ተመልክቷል።    

የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት አሰራር ተዘጋጅቶለት  ተጠያቂነትን ባሰፈነ መልኩ ማከናወን መቻሉ በርካታ ወጣቶች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሄደው በመሥራት ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ለመደገፍ በቅተዋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በሕገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳትና እንግልት በማስቀረት በኩል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

በቤት አያያዝ፣ በአሽከርካሪነት፣ በጤና ሙያተኝነትና በሌሎች የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ ሰርተው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በ2017 የበጀት ዓመትም በክልሉ 85 ሺህ በላይ ዜጎች ተገቢውን ሙያዊ ሥልጠና አግኝተው ወደ ተለያዩ ሀገራት በህጋዊ መንገድ ሂደው ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም