ኢንስቲትዩት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያከናወናቸውን ሃምሳ ስድስት የምርምር ውጤቶች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ተደራሽ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያከናወናቸውን ሃምሳ ስድስት የምርምር ውጤቶች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ተደራሽ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያከናወናቸውን ሃምሳ ስድስት የምርምር ውጤቶች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ተደራሽ ማድረጉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2013 ዓ.ም ከተመሰረተ ጀምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት አመርቂ እድገት አስመዝግቧል፡፡
በዘርፉ የወጣቶች ግንዛቤና ተሳትፎ እንዲጠናከር የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በፍጥነት እያደገ የሚገኘው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ እድሎችና ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ቢሆንም በአንፃሩ ለመረጃ ምንተፋም የተጋለጠ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ረገድ በዘርፉ የሚከናወኑ ምርምሮች የአንድ ሀገር ወይም ተቋም የወደፊት እድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን እያስገኘ ያለው ውጤት ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማደራጀት ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር ተችሏል፡፡
በዚህም ተቋሙ ተወዳዳሪ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለአብነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ 56 የምርምር ውጤቶችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ማሳተሙን አንስተዋል።
ከምርምር ውጤቶቹ መካከል ዘጠኙ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዳገኙ ጠቅሰው፤ ይህ ስኬት በሌሎች የምርምር ውጤቶችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢንጂነር ወርቁ (ዶ/ር) በርካታ ሀገራት በጤና፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነትን በእጥፍ በማሳደግ እና አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማዘመን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ የሀገሪቷና የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲያድግ፣ በትውልድ ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ ያለው የወጣቶች ግንዛቤና ተሳትፎ እንዲጠናከር የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት 200 ጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች በኢንስቲትዩቱ የስታርት አፕ ፕሮግራም ተካተው እየሰሩ እንደሚገኙ ጨምረው አስታውቀዋል።
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በዘርፉ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
'ኢንተሊጀንስ ለሁሉም' በሚል መሪ ሀሳብ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በሁሉም ዘርፎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።