ታላቁ ሩጫ አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነቷን የበለጠ እንድታልቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ሩጫ አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነቷን የበለጠ እንድታልቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ይበልጥ የቱሪስት መዳረሻነቷን እንድታልቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ነገ ሕዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር ውድድሩን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ ፤ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የከተማዋ ድምቀት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ለማህበራዊ መስተጋብር እና አብሮነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ውድድሩ አዲስ አበባን ለመላው ዓለም በስፋት ሲያስተዋውቅ መቆየቱን አስታውሰው በቀጣይም መዲናዋ የቱሪስት መዳረሻነቷን እንድታልቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።
በከተማዋ የአይን ማረፊያ የሆኑ ሰፋፊ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ገልጸው የውድድሩ ተሳታፊዎች መሰረተ ልማቶቹን ለመላው ዓለም እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ተወዳዳሪዎችን በመደገፍ ተጨማሪ ድምቀት እንዲፈጥሩም ጠይቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ቱሪዝምን በስፋት ለማስተዋወቅ እንደሚሰራና ለመሰል ስፖርታዊ ሁነቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።