ቀጥታ፡

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሰብል ዝርያ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

ሮቤ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን የአርሶ አደሩን ምርታማነት በሚያሳድግ የሰብል ዝርያ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ገለፀ። 

ማዕከሉ በምርምር ያወጣቸውን የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ከ210 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የመነሻ ዘር ብዜት እያከናወነ መሆኑም ተመልክቷል። 


 

የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ሚደቅሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ማዕከሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በምርምር እየደገፈ ነው። 


 

ለዚህም በበጀት ዓመቱ በተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ በአዝዕርት ጥበቃ፣ በእንስሳት መኖ፣ በቡናና ሻይ ልማት ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።  

በዞኑ ማዕከሉ እያካሄዳቸው ከሚገኙ አዳዲስ ምርምሮች በተጓዳኝ ባለፈው ዓመት የተለቀቁ አምስት የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከ210 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የመነሻ ዘር እያባዛ መሆኑን አስረድተዋል። 

እየተባዙ የሚገኙ የተሻሻሉ ዝርያዎች ከነባሩ ጋር ሲነፃፀሩ ከ10 በመቶ በላይ ምርታማነትን የሚጨምር መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት በአገዳና ብርዕ፣ በጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት ለአርሶ አደሩ ማድረሱን የገለጹት ደግሞ በማዕከሉ የሰብል ልማት የሥራ ሂደት ባለቤትና የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ታደለ ታደሰ ናቸው። 


 

የተሻሻሉ ዝርያዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡና የመሬትን ለምነት የሚመልሱ በመሆናቸው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጋቸውን አስረድተዋል። 

በማዕከሉ የሰብል በሽታ ተመራማሪ አቶ ዳኜ ኮራ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በሰብል ምርታማነት ላይ ማነቆ የሆኑ አረምና የአዝዕርት በሽታን ለመቆጣጠር በሚረጩ ኬሚካሎች አጠቃቀም ዙሪያ ምርምር በማካሄድ ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል። 


 

በተለይ በአሁኑ ወቅት የሰብል ራስን በማበስበስ ዘርፉን እየተፈታተነ በሚገኘው የ''ፉዛርዬም ሄድፕላይት'' በሽታ ዋና የምርምራቸው ትኩረት መሆኑንም አንስተዋል። 

የሲናና ወረዳ አርሶ አደር ሐብታሙ ግርማ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር የአካባቢው የስንዴ ዝርያ የሚያገኙት ምርት ከ20 ኩንታል እንደማይበልጥ አስታውሰዋል። 


 

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ከማዕከሉ የሚለቀቁ ምርጥ ዝርያዎችን በባለሙያ እገዛና የግብርና አሰራሮችን በመተግበር ምርታማነታቸውን ወደ  70 ኩንታል በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል እስካሁን 116 የሚሆኑ የሰብልና የእንስሳት መኖና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮሩ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ ለተጠቃሚው ማሰራጨቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም