ቀጥታ፡

ፍትኃዊና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ፍትኃዊና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የመስጠት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ገለጹ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የፍትሕ ዘርፉን አሠራር ለማሻሻል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

በዚህም የዳኝነት አገልግሎቱን ፍትኃዊ፣ ምቹ፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፤ በርካታ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶችና ማሻሻያዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል። 

ዳኞች ነፃ ሆነው የዳኝነት ሥራቸውን መሥራት እንዲችሉ ያለመከሰስ መብታቸው መከበሩን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የተቋማትን የሙያ ነፃነት ባከበረ መልኩ በጋራ ለፍትሕ የሚሠራበትን ሁኔታ መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።

ተገልጋዮች ከርቀት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዳይመላለሱ ከተዘዋዋሪ ችሎት ባሻገር ቋሚ ምድብ ችሎቶችን በማደራጀት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የተዘዋዋሪና ቋሚ ችሎት ዋናው ዓላማ በሩቅ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በሚቆጥብ መንገድ በአቅራቢያቸው የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።

በሌላ መልኩም ለኅብረተሰቡ በአቅራቢያው አገልግሎት ማግኘቱ አላስፈላጊ እንግልትና ወጪን የሚያስቀር በተለይ የአቅመ ደካሞችን ውጣ ውረድ ከመቀነስ አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር የተገልጋዮችን እንግልት ለመቀነስ በዲጂታል መንገድ ፋይል የሚከፈትበት አቤቱታ የሚቀርብበት እንዲሁም ክርክሮችን የሚከታተልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም