የተቀናጀ የግብርና መካናይዜሽንን በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ የግብርና መካናይዜሽንን በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡- በተቀናጀ የግብርና መካናይዜሽን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻለ ውጤት መገኘቱን የጉራጌ ዞን እና የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤቶች ገለጹ።
አርሶ አደሩ የምግብ ሉዓላዊነቱን እንዲያረጋግጥ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከሀገሪቱ የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ እና በጉራጌ ዞን የጤፍ እና የበቆሎ ክላስተር፣ የተቀናጀ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳን ጎብኝተዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አበራ ወንድሙ በዞኑ 150 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር ወቅት በልዩ ልዩ ሰብሎች ማልመት መቻሉን ተናግረዋል።
በዞኑ አብዛኛው ሰብል በኩታ ገጠም መልማቱን የገለጹት አቶ አበራ፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም እየሰፋ የመጣውን የአፈር አሲዳማነት ለመከላከል 30ሺህ ኩንታል የአፈር ማከሚያ ኖራ ቀርቦ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል ።
አርሶ አደሩን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ የመስኖ አማራጮችን በመጠቀም በዓመት ሶስት ጊዜ እንዲያመርት በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።
እንዲሁም በየአካባቢው ለኤክስፖርት የሚሆኑ እንደ ቦሎቄና ሮዝመሪ ያሉ የግብርና ምርቶች እየተስፋፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
አርሶ አደር መኪዮ ነጋሽ እና አብዱልፈታህ ጀማል በክላስተር ማምረት በመጀመራቸው የተሻለ ምርት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የእለት ምግባችንን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችለናል ሲሉ ገልጸዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አብዲሽኩር ደሊል የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተቀናጀ ግብርና የጤፍ እና የበቆሎ ክላስተር በማደራጀት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በበቆሎ ክላስተር በሞዴል አርሶ አደር በሄክታር እስከ 110 ኩንታል ምርት ማምረት እንደተቻለ ተናግረዋል።
እንዲሁም በሁሉም ቀበሌዎች የጤፍ ክላስተርን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በአትክልትና ፍራፍሬ 30:40:30 በሚል በተጀመረው ኢኒሼቲቨ የፍራፍሬ መንደር መፍጠር መቻሉን ነው ሃላፊው የገለጹት።