የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ለትምህርት ሴክተሩ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ለትምህርት ሴክተሩ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዳማ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፦በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ለትምህርት ሴክተሩ እድገትና ማንሰራራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የምስራቅ ሸዋና እና የአዳማ ከተማ አስተዳደር የትምህርት አመራሮች ተናገሩ።
በዞኑ እና በከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ የተገኘውን ውጤት በሚመለከት ኢዜአ የምስራቅ ሸዋና እና የአዳማ ከተማ አስተዳደር የትምህርት አመራሮች አነጋግሯል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግርማ ለማ፤ በተያዘው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ለማነቃቃት ከተያዘው ቁልፍ ተግባር አንዱ የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ዘንድሮ በዞኑ በ744 ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ መጀመሩን ተናግረዋል።
በቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶችም የምገባ መርሃ ግብሩን ለመጀመር የሚያስችል የዝግጅት ስራ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በትምህርት ቤቶች ምገባ መጀመሩ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ በእጅጉ የቀነሰ፣ የትምህርት ተሳትፎ እና የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ያሳደገ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ለትምህርት ሴክተሩ እድገትና ማንሰራራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተስፋዬ፤ የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር በትምህርት ዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እያመጣ ያለ ምርጥ ተሞክሮ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ አምና በ32 ቅድመ መደበኛና በ64 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብሩ መጀመሩን አስታውሰው ዘንድሮም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም የተማሪዎች ጤና እንዲጠበቅ፣ የትምህርት አቀባበላቸው እንዲያድግና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ትግበራ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ አልሚ ባለሀብቶች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ሌሎችም የተሳተፉበት መሆኑን ገልጸው ትብብርና ተሳትፏቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።