ቀጥታ፡

በዞኑ ህጋዊ የንግድ ስርዓት የማጠናከር ተግባር ውጤት እያመጣ ነው

ጭሮ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ባለፉት አራት ወራት ባለ ድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተሰራው ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን የማጠናከር ተግባር ውጤት ማምጣቱን የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡

በዞኑ በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው በተገኙ 154 ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱም ተመላክቷል። 

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ጀማል ቃሲም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በበጀት ዓመቱ የንግድ ስርዓቱን ጤናማ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ህገወጥ የንግድ ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።

በዞኑ ህገወጥ የንግድ ተግባራትን ለመግታትና ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ለማጠናከር ማህበረሰቡን በማሳተፍና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። 

በዚህም መሰረት ባለፉት አራት ወራት በጭሮ፣ በሂርና፣ በገለምሶ በበዴሳ እና መቻራ ከተሞች ውስጥ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ፣ የዋጋ ዝርዝር ባልለጠፉ፣ ኮንትሮባንድ በማዘዋወር፣ የነዳጅ ግብይቱን ከኤሌክትሮኒክስ ሽያጭ ውጪ በፈጸሙና በሌሎችም ላይ ህጋዊና አስተዳደረዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።  

በዚህም በዞኑ በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው በተገኙ 154 ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።  

ከኤሌክትሮኒክስ ሽያጭ ውጪ የነዳጅ ግብይት የፈጸሙ አምስት የነዳጅ ማደያዎች ሲሆኑ 149 ነጋዴዎች ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው ነጋዴዎች ከድርጊታቸው ታርመው ህጋዊ መስመር ተከትለው ወደ ስራቸው እንዲገቡ  የተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞኑ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ለማጠናከር ባለፉት ሶስት ወራት በ15 ወረዳዎች ለሚገኙ 6 ሺህ 232 ነጋዴዎች  የግንዛቤ ማስጨበቻ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከ17 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ህጋዊ የግብር ከፋይነት መታወቂያ ወስደው በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም