የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አገልግሎቱን ከከተማዋ ዕድገት ጋር አጣጥሞ የማሳደግ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አገልግሎቱን ከከተማዋ ዕድገት ጋር አጣጥሞ የማሳደግ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አገልግሎቱን ከከተማዋ ዕድገት ጋር አጣጥሞ ለማሳደግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በብቁ የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
አዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ፖሊስ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ አቅም ያሠለጠናቸውን እጩ መኮንኖች አስመርቋል።
በምረቃው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የአስተዳደሩ ዋና ትኩረት የከተማዋን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ አቅም መገንባትና ማህበራዊ ህይወት በማሻሻል ዘላቂ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየመለሰ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው።
ከተማዋን ለኑሮና ለሥራ የተመቸች እንድትሆን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተመራጭ የኮንፍረንስ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በውጤታማነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
እነዚህን የልማት ሥራዎችን ዘላቂ ለማድረግ ሠላምና ደህንነት ማረጋገጥ ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የከተማዋን ሠላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለው የለውጥ ሥራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ መምሪያው በከተማዋ ያለውን እድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ አገልግሎቱን ለማሳደግ ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በብቁ የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።ይህም ፖሊስ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈጸም እያስቻለው መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ መምሪያው ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትን ጨምሮ በቴክኖሎጂ ራሱን በማደራጀት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅና ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ተመራቂ መኮንኖች በከተማዋ ሰላምንና ደህንነትን ከማስጠበቅ አንጻር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተው፤ በከተማዋ ህግና ስርዓት በማስከበር ረገድ ቁርጠኛ ሆነው እንዲሰሩ አሳስበዋል።