ቀጥታ፡

ፋብሪካው አዳዲስ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችን ወደ ምርት ሂደት ሊያስገባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 13/2018 (ኢዜአ)፡-በስኳር ይዘታቸው ከነባሮቹ ዝርያዎች የተሻሉ በምርምር የለሙ ሰባት አዳዲስ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችን ወደ ምርት ሂደት ሊያስገባ መሆኑን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ አስታወቀ።

የምርምር ሂደታቸው ተጠናቅቆ በዘር ደረጃ ተባዝተውና ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ ከተለዩት አዳዲስ የሸንኮራ አገዳ ዝርዎች መካከል አራቱ ሀገር በቀል መሆናቸውን በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የምርምርና ሥርፀት አገልግሎት ኃላፊ አምሮቴ ተክሌ ለኢዜአ ተናግረዋል።

እነዚህ ሀገር በቀል ዝርያዎችም፤ ኤል -151 (ነጭ አገዳ)፣ ኤል - 153 (የበስኩላ ሸንኮራ)፣ ኤል -159 (ነጭ ሸንኮራ) እና ኤል - 422 መሆናቸውን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ሦስቱ ከፈረንሳይ የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው እነሱም፤ ፒ ኤስ አር - 97092፣ ኤፍ ጂ - 04298፣ ኤፍ ጂ- 04197 የተሰኙ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዝርያዎቹ በጥሩ የዘር አገዳ ጊዜ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዘንድሮው የተከላ ወቅት በማልማት አባዝቶ ወደ ምርት አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ ይችላል ብለዋል።

አዳዲሶቹ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች በሚደርሱበት ጊዜ ፍጥነት፣ በሽታን ተቋቁሞ በየትኛውም ሥነ-ምኅዳር በመላመድ እና በስኳር ይዘታቸው ከነባሮቹ ዝርያዎች የተሻሉ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እዩኤል ለላንጎ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ቀደም ሲል ከሚጠቀማቸው ዘጠኝ በምርት ሂደት ያሉ የሸንኮራ አገዳ ዝርዎች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ሦስቱ ብቻ መሆናቸውን አንስተዋል።

ስለዚህ የሸንኮራ አገዳ የዝርያ ዓይነቶች ውስንነት የስኳር ኢንዱስትሪው መሠረታዊ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ አንጻር የአዳዲሶቹ ዝርያዎች የምርምር ሂደት ተጠናቅቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር በስኳር ኢንዱስትሪው የሚስተዋለውን መሠረታው የሸንኮራ አገዳ የዝርያ ዓይነቶች ውስንነት ይቀንሳል ብለዋል።

አዳዲሶቹን ሰባት የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች የምርምር ሥራ ያከናወኑት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የምርምር እና ስልጠና ዘርፍ እና ወንጂ ስኳር ፋብሪካ በጋራ በመሆን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም